በሐረሪ ክልል ወደ ልማት ያልገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ተሰረዘ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ልማት ባልገቡ ባለሃብቶች ላይ ፈቃድ እስከመሰረዝ የደረሰ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ሃላፊ አቶ ኡስማኢል ዩስፍ÷ የክልሉን ልማት ለማፋጠን ባለሃብቱም የድርሻውን እንዲወጣ ለማስቻል በሚል ግንዛቤ የመስጠት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም የባለሃብቶች እንቅሰቃሴ ያለበትን ሁኔታ የተቋቋመው ኮሚቴው ለሶስት ጊዜያት የመስክ ምልከታና የልየታ ስራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም በክልሉ በኢንቨስትመንት አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ መሰረት ቀደም ሲል የኢንቨስትመንት ፍቃድና መሬት ወስደው ወደ ሥራ ባልገቡና ግንባታ ያጓተቱ 112 ባለሃብቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።
በተወሰደው እርምጃም የ8 ባለሃብቶች ፈቃድ ሲሰረዝ÷ በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መታገድና ማስጠንቀቂያ የመስጠት እርምጃ መወሰዱን ለኢዜአ አብራርተዋል።
ወደ ልማት ባልገቡ ባለሃብቶች ላይ ከሚወሰደው እርምጃ ጎን ለጎንም ባለሃብቶቹ የሚያጋጥማቸውን ችግሮችንም የማቃለል ሥራም ተከናውኗል ብለዋል።
በባለሃብቶቹ ላይ እርምጃ መወሰድ መጀመሩም ሌሎች የፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራዎች እንዲፋጠኑ እድል መፍጠሩን አመልክተዋል።
በበጀት ዓመቱ በክልሉ ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 82 ባለሃብቶች የኢንቨስተመንት ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።