ማሰልጠኛ ማዕከሉ ያሰለጠናቸውን የተዋጊ መሃንዲስ ባለሙያዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን የተዋጊ መሃንዲስ ባለሙያዎች አስመርቋል፡፡
በምረቃ መርሃ ግብሩ የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሰለሞን ኢተፋ÷መከላከያ ሠራዊቱ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የጥፋት እሳት በመለኮስ ሠላምን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አሸባሪ እና ፅንፈኛ ቡድኖችን በመደምሰስ ዕኩይ አላማቸውን ትርጉም ወደሌለው ደረጃ ማውረዱን ገልጸዋል።
ተመራቂ የመሃንዲስ ባለሙያዎች በስልጠና ያገኙትን ክህሎት በማያቋርጥ ትጋት እያጎለበቱ የራሳቸውን እና የሌሎችን አባላት አቅም በማጠናከር ድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ሠልጣኞች የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ፣ በሠራዊት መስፈን ያለባቸው እሴቶች፣ የአካል ብቃት፣ ለመሀንዲስ ስኬታማ የግዳጅ አፈፃጸም የሚረዱ ስልጠናዎች መውሰዳቸውን የማሰልጠኛው ዋና አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ቦጋለ ተገኔ ገልጸዋል።
ማሰልጠኛ ማዕከሉ በተለያዩ ወታደራዊ ዘርፎች ጀግኖችን ከማፍራት ግዳጁ ባለፈ ለማህበረሰባዊ አገልግልቶች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡