የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን ምስል በአለም አቀፍ ደረጃ በበጎ የሚያመላክት መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን ምስል በአለም አቀፍ ደረጃ በበጎ የሚያመላክት መሆኑን የታሪክ መምህርና ተመራማሪዉ ተባባሪ ፕሮፌሰር ከተቦ አብዲዮ ተናገሩ።
አሁን ላይ ግንባታው 74 በቶ የደረሰው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በግድቡ የግንባታ ሂደት ዙሪያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ፥ የዋናዉ ግድብ ኮንክሪት ሙሊት ስራ በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ግድቡ በመጀመሪያውን ሃይል ማመንጨት የሚያስችለዉ እና ውሃ የሚተኛበትን ቦታ ለማመቻቸት የደን ምንጣሮ ዝግጅት እንደተጠናቀም ነው ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ያነሱት።
አሁን ላይ አጠቃላይ ግንባታው 74 በቶ የደረሰዉ ታላቁ የህዳሴ ግድብ፤ የብረታብረት ፣የኤሌክትሮ መካኒካል እና ሌሎች ስራዎች እየተከናወኑለት ይገኛል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሃገራዊ አንድነትን ከማረጋገጡ ባሻገር፣ አፍሪቃዉያንን የሚያስተሳስር አሻራ እንደሚሆን ይታመናል።
በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክ መምህርና ተመራማሪዉ ተባባሪ ፕሮፌሰር ከተቦ አብዲዮ፥ የግድቡ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን ምስል በአለም አቀፍ ደረጃ በበጎ የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ግድቡ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ መሆኑ የኔነት ስሜትን ፈጥሯል ያሉ ሲሆን፥ አባይ ከኢትዮጵያውያን ባሻገር አፍሪካውያንን የሚያገናኝ ቅርስ እንደሆነም ተባባሪ ፕሮፌሰር ከተቦ አብዲዮ ተናግረዋል።
በአወል አበራ