Fana: At a Speed of Life!

በደርባን የኢትዮጵያያ ዳያስፖራ አባላት ለ #ጽዱኢትዮጵያ ንቅናቄ የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ አፍሪካ ደርባንና አካባቢው የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ለ #ጽዱኢትዮጵያ ንቅናቄ ማስፈጸሚያ የሚውል 410 ሺህ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የዳያስፖራ አባላቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በይፋ ያቀረቡትን የ #ጽዱኢትዮጵያ ንቅናቄ የድጋፍ ጥሪ በመቀበል ነው ድጋፍ ያደረጉት፡፡

ድጋፉ ይፋ የተደረገው ኤምባሲውና በደርባን የድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ በጋራ ባዘጋጁት ፕሮግራም ላይ ሲሆን÷ ኮሚቴው ድጋፉን በፍጥነት አሰባስቦ ገቢ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር)÷ በደቡባዊ የአፍሪካ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የዳያስፖራ አባላት ከሀገራቸው ጋር ያላቸው ትስስርና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሀገር ግንባታ የልማት እንቅስቃሴዎችና በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለሚቀርቡ የተሳትፎ ጥሪዎች ወቅታዊና ተጨባጭ ምላሽ በመስጠት ታሪካዊ አሻራቸውን በደማቅ ቀለም እያሳረፉ ይገኛሉም ነው ያሉት፡፡

አምባሳደሩ በደርባንና አካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለ #ጽዱኢትዮጵያ ንቅናቄ ማስፈጸሚያ ላበረከቱት ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

በመላው ደቡብ አፍሪካና በሌሎች ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ለ #ጽዱኢትዮጵያ ንቅናቄ፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ለሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.