የአረንጓዴ ዐሻራ አንዱ ግብ የለም አፈር መሸርሸርን ማስቀረት ነው – ጠ/ ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ አንዱ ግብ የለም አፈር መሸርሸርን ማስቀረት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ።
የደን ምንጣሮ እና የአየር ንብረት ለውጥ ከሌሎች መንሥኤዎች ጋር ተዳምረው በየዓመቱ በኢትዮጵያ የለም አፈር መሸርሸርን ያስከትላሉ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት የአረንጓዴ ዐሻራ አንዱ ግብ ይህንን እጦት መቀልበስ ነው።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በረሃማነትን እና ድርቅን ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶችን በሚያከብርበት በዚህ ዕለት ሁላችንም በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ እንቅስቃሴ እንሳተፍ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የ2012 የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ መርሐ ግብር በይፋ የተጀመረ ሲሆን በዘንድሮው የክረምት ወቅት 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።
በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊየን ዛፎችን ለመትከል ያቀደችው ሀገሪቱ አምና በሀገር አቀፍ ደረጃ 20 ሚልየን ዜጎች በተሳተፉበት ዘመቻ 4 ቢሊዮን ችግኞችን ተክላለች።
መንግስት ከእነዚህ ችግኞች መካከል በአጠቃላይ 84 በመቶ የሚሆኑት መፅደቃቸውን ነው ያስታወቀው።