Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል “ትምህርት ለትውልድ” ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ “ትምህርት ለትውልድ” የተሰኘ ክልላዊ ንቅናቄ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው፡፡

በንቅናቄ መድረኩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የትምህርት ሚኒስትር ዴዔታ አየለች እሸቴና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የክልሉ የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)÷ ንቅናቄው በክልሉ የትምህርት ሥራ የገጠመውን ስብራት ተረድተን ለመጠገንና የትምህርት ሥርዓቱን በስኬት ለመተግበር የሰው ሃይል ግንባታን ለማስቀጠል ያለመ ነው ብለዋል።

ክልሉ ከነበረበት የትምህርት ቤቶች የመሰረተ ልማት ችግር በተጨማሪ በክልሉ ውስጥ የተፈጠረው ግጭት በብዙ የክልሉ አካባቢዎች የትምህርት ሥራውን እንዳስተጓጎለው አንስተዋል።

አሁን ላይ በክልሉ ከ3 ሺህ በላይ ት/ቤቶች መዘጋታቸውን ጠቁመው÷ በእነዚህ ት/ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎችና መምህራን ከትምህርትና ከሥራ ገበታቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ የትምህርት ሥራ የገጠመውን ፈተና በድል ለመወጣት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከሚሠራው ሥራ ጎን ለጎን ት/ቤቶች የጎደለባቸውን መሰረተ ልማት ማሟላት እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

አዳዲስ ግንባታዎችን በመሥራት የት/ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ የተማሪዎችን ምገባ ማስጀመርና አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት መተግበር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው÷የአማራ ክልል ለትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ማኅበረሰብ ያለበት ክልል መሆኑ ለትምህርት ሥራችን እንደ አንድ መስፈንጠሪያ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

የሰሜኑ ጦርነት እና ኮቪድ-19 እንዲሁም አሁን በክልሉ ውስጥ የተፈጠረው ችግር የነበርንበትን የትምህርት ሥራ አስጠብቀን ለመሄድ እንቅፋት ሆኖብናል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

በቀጣይ የትምህርት ተቋማት ያሉበትን ደረጃ ማወቅ፣ ግብዓት ማሟላት፣ ተጨማሪ ክፍሎችን መገንባትና አዲሱን የትምህርት ሥርዓት በውጤታማነት መተግበር እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በደሳለኝ ቢራራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.