ተሽከርካሪ በመስረቅ በተጠረጠረችው ግለሰብ ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ተሽከርካሪ በመስረቅ በተጠረጠረችው ግለሰብ ላይ ክስ መመስረቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ግለሰቧ በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት መቅረቧም ነው የተመላከተው፡፡
ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ቢጫ ፎቅ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ መኪና በመስረቅ ተጠርጥራ በፖሊስ ክትትል የተያዘችው መና ከበደ፤ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ በመተላለፍ የማይገባትን ብልፅግና ለማግኘት ንብረትነቱ የግል ተበዳይ የሆነው የሰሌዳ ቁጥር 3 B 23912 አ/አ ተሽከርካሪ በመስረቋ ፖሊስ ምርመራውን አጣርቶ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ልኮ ክስ እንዲመሰረትባት ማደረጉን የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡
በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች ግለሰቧ ተለቃለች እንዲሁም ወንጀሉን ሳታውቅ ነው የፈፀመችው የሚሉ መረጃዎች እየተሰራጩ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
ይሁን እንጀ የግል ተበዳይ መኪናቸው መሰረቁን ለፖሊስ ያመለከቱ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ተጠርጣሪ ግለሰቧም ተሽከርካሪውን ለረጅም ሰዓት ይዛ መሰወሯ ታሳቢ በማድረግና ድርጊቷም በማስረጃ በመረጋገጡ ዐቃቤ ሕግ በተሽከርካሪ ስርቆት ክስ መመስረቱን ፖሊስ አስታውቋል፡፡