Fana: At a Speed of Life!

የክልሉን ህዝብ የልማት ጥያቄ ለመመለስ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የህዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

በርእሰ መስተዳድሩ የተመራና የክልሉና የፈዴራል ከፍተኛ አመራር አባላት የተካተቱበት ቡድን በቄለምና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች የልማት ስራዎችን እየጎበኘ ነው።

በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በ78 ሚሊየን ብር የተገነባ የጉሊሶ ሚኒ ሆስፒታልን አቶ ሽመልስ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት÷ የክልሉ መንግስት የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።

በምዕራብ ኦሮሚያ ህዝቡ በተለያየ ጊዜ ሲያነሳቸው የቆዩ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

የህዝብ የልማት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የክልሉ መንግስት የጀመራቸው የልማት ሥራዎች እንዲሳኩ ሰላምን ማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ህዝቡ የድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

የአሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር መንግስቱ በቀለ በበኩላቸው÷ የክልሉ መንግስት ህዝቡ ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች ዜጋ እንዲሆን በጤና ዘርፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በበጀት ዓመቱም ከ400 በላይ የህክምና ተቋማት ግንባታ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

የዚሁ ጥረት አካል የሆነው የሚኒ ሆስፒታሉ ምርቃት ባሻገር ከ140 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ለጉሊሶ ጤና ጣቢያ አገልግሎት የሚውል የተለያዩ የህክምና ቁሳቁስ እንዲሟላ መደረጉን አስታውቀዋል።

በምዕራበ ወለጋ ዞን የተገነባው ሚኒ ሆስፒታልም ከ125 ሺህ በላይ የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.