“የህዳሴ ግድቡ በወቅቱ በነበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አድራጊ ፈጣሪነት ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርጓል”- አምባሳደር ዓለማየሁ ተገኑ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2012 (ኤፍ. ቢ.ሲ) የህዳሴ ግድብ ግንባታ በወቅቱ ቦርድ ሰብሳቢ በነበሩት ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል አድራጊ ፈጣሪነት በፍጥነት ተዳክሞ ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርጓል ሲሉ የቀድሞው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና በሩሲያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዓለማየሁ ተገኑ አስታወቁ፡፡
አምባሳደር ዓለማየሁ ተገኑ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፥ የህዳሴ ግድቡ አቶ መለስ በህይወት እስከነበሩበት ጊዜ ድረስ በየወሩ ይገመገም የነበረ ሲሆን፥ ከእርሳቸው ህልፈት በኋላ በየወሩ መገምገሙ ቀርቷል፡፡
የወቅቱ የቦርድ ሰብሳቢ በክላስተር አደረጃጀት በሁለት ወር አንድ ጊዜ እንዲታይ ብለው አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን አስታውሰው ፥ ሰብሳቢው አሠራሩን ተግባራዊ ሳያደርጉ መቅረታቸውንም አመልክተዋል። በዚህ ሁኔታ የህዳሴ ግድቡን ፕሮጀክት የመብራት ኃይል ቦርድ አካልም ይገመግመው እንዳልነበር ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱን በሚመለከት በየጊዜው ለቦርዱ ጥያቄ እናቀርብ ነበር ያሉት አምባሳደር አለማየሁ፥ ቦርዱም ገምግሞ ወደ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የግምገማውን ውጤት አይልክም ነበር ነው ያሉት። የዘርፉ ባለቤት ብንሆንም ተገልለን ነበር፤ ሪፖርትም ከመብራት ኃይል እየወሰድን ጉድለቶቹን እንናገር ነበር ሲሉም አስረድተዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከመብራት ኃይል የሚያገኘውን መረጃ ይዞ እንደ ዘርፍ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት እንኳን “ምን አግብቷችሁ ነው መግለጫ የምትሰጡት” በማለት በቦርድ ሰብሳቢው በኩል ቁጣ ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ሁኔታም ፕሮጀክቱ ከህዝብ ፕሮጀክትነቱ ወርዶ የአንድ ግለሰብ ፕሮጀክት ሆኖ እንደነበር አመልክተዋል። ይህም የግድቡን ግንባታ ለውድቀት ከመዳረጉ ባለፈ “በአገራችን ታሪክ የሚያሳዝን ድርጊት ሆኖ አልፏል” ብለዋል፡፡
በወቅቱ የህዳሴ ግድቡ ሥራና ውሳኔዎች በሰብሳቢው ውሳኔ ስር የነበሩ መሆናቸው ትክክል እንዳልሆነ ለቦርድ አባላት ቢነገርም የቦርድ አባላትም ፕሮጀክቱን እንደማይገመግሙ ማስታወቃቸውን አመልክተው፤ ግንባታው በአካል ባለመገምገሙ ብቻ ትልቅ ውድቀት እንደነበር ገልጸዋል።
በወቅቱ የነበረውን ቦርድ ችግሮች በሚገባ ለማየት አሁን የተቀየረው ቦርድ በአጭር ጊዜ ያመጣውን ለውጥ ማየት አሳማኝና በቂ ነው ብለዋል።
“ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ከግለሰብ እጅ ወጥቶ ወደ ህዝባዊነቱ ተመልሷል፡፡ አገግሞና የኮንትራት አስተዳደሩም ተለውጦ አስደናቂ ለውጥ በማምጣት ዳግም አገራዊ ተስፋ ፈጥሯል” ብለዋል፡፡