Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና የብራዚልን የንግድ ሚዛን ለማሻሻል እንደሚሰራ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ወደ ብራዚል የምትልካቸውን ምርቶች መጠን በማሳደግ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ሚዛን ለማሻሻል በቅንጅት እንደሚሰራ የንግድና ቀጣናዊ ትስስትር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ከብራዚል ልኡካን ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነትና የንግድ ልውውጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ብራዚል የብሪክስ አባል እንደመሆናቸው የንግድ ግንኙነታቸውንና ወዳጅነታቸውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወደ ብራዚል የሚላኩ ምርቶችን በማሳደግ እንዲሁም ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ባላት እምቅ ሀብት ብራዚላዊያን መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነትን ይበልጥ ማጎልበት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡

በውይይቱ በቁም እንሰሳት ንግድ ዘርፍ ከብራዚል ልምድ ለመውሰድ፣ በግብርናው እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በጋራ ለመስራት እና ግንኙነታቸውን ለማጎልበት በቀጣይነት ለመመምከርና ስምምነቶችን ለመፈራረም ተግባብተዋል።

በተመሳሳይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ እያሱ ኤልያስ (ፕ/ር) ከብራዚል የግብርናው ዘርፍ አመራሮች ጋር በዘርፉ በሁሉም መስኮች በተለይም በተፈጥሮ ሀብት ልማት በሚከናወኑ ተግባራት ላይ በትብብር ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.