የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ፣ የባሕር ኃይልና የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል የክረምት በጎ ፈቃድን አስጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር መከላከያ ሰራዊት የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ፣ የባሕር ኃይልና የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል የጦር ክፍሎች የክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ-ግብርን በይፋ አስጀመሩ።
በመርሐ ግብሩ የዕዙ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ፣ የባሕር ኃይልና የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል ተወካዮችን ጨምሮ የመከላከያ ጀኔራል መኮንኖችና የሰራዊቱ አባላት ተገኝተዋል።
የክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብሩ “ከካምፓችን ወደ ሕዝባችን” በሚል መሪ ሐሳብ ከሐምሌ 1 እስከ 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የበጎ ፈቃድ ስራው ከካምፕ ጀምሮ እስከ ህብረተሰብ የሚዘልቅ አካባቢን ውብና ፅዱ ማድረግን ያካተተ ነው፡፡
በአረንጓዴ ልማት ረገድም ከዚህ በፊት የነበረውን ልምድ በማጠናከር ይበልጥ በአርአያነት ይሰራል ብለዋል።
የአቅመ ደካሞችን ቤት ዕድሳት በተመለከተም ከሰራዊቱ የወጡና የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ አባላት ቤተሰቦችን ማገዝ የመርሐ-ግብሩ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
ሰራዊቱ ባለበት ሁሉ የደም ልገሳን ጨምሮ በመርሐ-ግብሩ በጎ ስራውን እንዲያጎለብት ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።