Fana: At a Speed of Life!

በቄለም ወለጋ ላሎ ቂሌ ከተማ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቄለም ወለጋ ዞን ላሎ ቂሌ ከተማ ከ121 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡

ፕሮጀክቱን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ መርቀው ሥራ አስጀምረውታል።

አቶ አወሉ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት÷የክልሉ መንግሥት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያካሄዳቸው የነበሩትን ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ አድርጓል።

የላሎ ቂሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ጨምሮ በዞኑ ለአገልግሎት የበቁ የመሠረተ ልማት ተቋማትም በዚያው መሠረት ግንባታቸው ሲከናወን መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች በመመለስ የበለጸገችና የለማች ሀገርን ለትውልድ ለማውረስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ፕሮጀክቱ ረጅም ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ ሕዝቡ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግለት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገመቹ ጉርሜሳ በበኩላቸው÷በዞኑ የ875 ፕሮጀክቶች ግንባታ ሲካሄድ መቆየቱን ጠቁመው የላሎ ቂሌ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የሕዝቡን ችግር ለማቃለል የተገነባ መሆኑን አስረድተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.