የምክር ቤት አባላት ከ127 ሺህ በላይ ቀበሌዎች የሰበሰቧቸውን ጥያቄዎች ለተቋማት አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተመረጡባቸው አካባቢዎች ወርደው 127 ሺህ 277 ቀበሌዎች ላይ የሰበሰቧቸውን ጥያቄዎች ለአስፈጻሚ ተቋማት ለይተው አቅርበዋል፡፡
አስፈፃሚው አካል ለህዝብ ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳስቧል፡፡
ከህዝብ በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
የምክር ቤት አባላትም በተመረጡባቸው አካባቢዎች ወርደው ከ127 ሺህ 277 ቀበሌዎች የሰበሰቧቸው ጥያቄዎችም ለተቋማት ተለይተው ቀርበዋል።
የሰላም እጦት፣ የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ የመሰረተ ልማትና ፕሮጀክቶች መጓተት፣ የህዝብ ጥያቄዎችን አለማዳመጥ፣ የሚነገረውና መሬት ላይ ያለው መለያየት ዋና ዋና ጥያቄዎች መሆናቸውን በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴዔታ መሰረት ኃይሌ ተናግረዋል።
በተቋማቱ በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ነው።
በዚሁ ወቅት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)÷ ለህዝብ ጥያቄዎች መመለስ መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የህብረተሰቡ ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው የፀጥታ ችግር በተፈለገው ያህል የአፈር ማዳበሪያ ለማድረስ እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል።
ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮችን ተጠቅሞ የተገዛውን ማዳበሪያ የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ መሆኑንና የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በእጀባ እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ማዳበሪያ እጥረት ችግር የማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ አዳዲስ የግዥና የማጓጓዝ ስርአቶች እየተዘረጉ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታየውን የሀብት ብክነትና ሙስና ለማስቆም እስካሁን የ6 ተቋማት አመራሮች መነሳታቸውን ጠቅሰው፤ በመጪ ሳምንታትም የ4 ተቋማት አመራሮች እንደሚነሱ ጠቁመዋል።
በአፈወርቅ እያዩ