የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ በመጀመሪያ አጀንዳ በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመነት በተለይም ገበያ ተኮር በሆኑ የቡና እና የቅባት እህል ምርት እንዲሁም ዘመናዊ የእንስሳት ሃብት ልማትና መኖ አቅርቦት ማሳለጥ የሚያስችሉ 25 ፕሮጀክቶችን መርምሮ 23ቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ ወስኗል፡፡
በመቀጠል የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያ አካል የሆነውን የባህል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋምና እውቅና ለመስጠት የወጣውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለክልሉ ምክር ቤት መርቷል፡፡
እንዲሁም በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ አጋር ድርጅቶች የተገነቡ የመስኖ እና የድሬይኔጅ መሠረት ልማቶችን ለተጠቃሚዎች በማስተላለፍና ማስተዳደር የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል የክልሉ የመስኖ ውሃ ተጠቃሚዎች ማህበራት ረቂቅ አዋጅን ተወያይቶ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲመራ ወስኗል፡፡
በመጨረሓም የ2017 በጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲመራ መወሰኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡