ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሠላም የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ የአውሮፓ ህብረት ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዋ አኔት ዌበርን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን÷ በተለይ በሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመሩ ጥረቶች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት ህብረቱ እንደሚደግፍም ልዩ መልዕክተኛዋ ተናግረዋል፡፡
በሱዳን ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች በአፍሪካዊ ማዕቀፍ መከወን እንዳለባቸው በውይይቱ ላይ መነሳቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኃላፊዎቹ በሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታና በሌሎች የአፍሪካ ቀንድና ቀይ ባህር ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ላይም ውይይት አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያና አውሮፓ ህብረት ስትራቴጂያዊ ግንኙነትን ለማሳደግ ምክክሮችን ማጠናከር እንደሚገባ በውይይቱ ተገልጿል፡፡