Fana: At a Speed of Life!

የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎችን በመስረቅ ወንጀል የተጠረጠሩ 18 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎችን በመስረቅ እና በመሸሸግ ወንጀል የተጠረጠሩ 18 ግለሰቦች ከነንብረቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የወንጀል ድርጊቱ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ቁስቋም ማርያም አካባቢ የግል ተበዳይ ተሽከርካሪያቸውን በራሳቸው ጋራዥ ውስጥ አቁመው በነበረበት አጋጣሚ ነው የተፈጸመው፡፡

የደረቅ ጭነት ማመላለሻ የሆነውና 4 ሚሊየን ብር የዋጋ ግምት ያለው “አይቪኮ ትራከር” ጋራዡ ውስጥ ቆሞ በነበረበት ወቅት የጋራዡ አንድ የጥበቃ ሰራተኛ ከሌሎች 4 ግብራበሮቹ ጋር በመመሳጠር ተሽከርካሪውን ሰርቀው መውሰዳቸው ተገልጿል፡፡

የግል ተበዳዩ ተሽከርካሪ ጥገና የሚከናወንበት ጋራዣቸውን የቦታ ለውጥ ለማድረግ በሒደት ላይ የነበሩ ሲሆን÷በዚሁ ሒደት ወደ ሌላ ቦታ ለመጓጓዝ በከባድ ተሽከርካሪያቸው ላይ ጭነዋቸው የነበሩ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው የተለያዩ የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች አብረው መወሰዳቸው ታውቋል፡፡

ፖሊስ ባደረገው ክትትል የጥበቃ ሰራተኛውን እና አራቱ ግብራበሮቹን በሸገር ከተማ ኮዬ ንፋስ ስልክ አካባቢ መኪናውን ለመሸጥ ሲደራደሩ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ በማጣራት በዓቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸዋል ፡፡

የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎቹን የገዙ እና የሸሸጉ 13 ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን÷ የተሸጡ ዕቃዎችን በማስመለስ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝም የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.