ዩኒቨርሲቲዎች የሁለተኛ ዙር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችን መቀበል ጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩኒቨርሲቲዎች የ2016 ትምህርት ዘመን የተፈጥሮ ሳይንስ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎችን መቀበል ጀምረዋል፡፡
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በሁለት ዙር የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና እንዲወስዱ 26 ሺህ 973 ተፈታኝ ተማሪዎች በትምህርት ሚኒስቴር እንደተመደቡ ተገልጿል፡፡
የመጀመርያ ዙር የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ፈተናውን አጠናቀው ወደየመጡበት አካባቢ እንደተመለሱም ተጠቁሟል፡፡
በዩኒቨርሲቲው በሁለተኛው ዙር በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ከ14 ሺሕ የሚበልጡ ተማሪዎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
እንዲሁም በመቱ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችን የመቀበል ስራ መጀመሩ ተጠቅሷል፡፡
ለሁለተኛው ዙር ፈተና የተመደቡ ተማሪዎች በዛሬው ዕለት ወደ ዩኒቨርሲቲዎች መግባት እንደጀመሩ ከየዩኒቨርሲቲዎች የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ከሐምሌ 9 እስከ 11 ቀን 2016 ዓ.ም በበይነ መረብ እና በወረቀት ፈተናው ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡