የአውቶቡስ መስመሮችን የጣሱ ከ15 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ተቀጥተዋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአውቶቡስ ተብለው የተሰመሩ መስመሮችን ጥሰው የገቡና ደንብን የተላለፉ ከ15 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች እንዲቀጡ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ገለጸ፡፡
በባለስልጣኑ የትራፊክ ቁጥጥርና ኩነት አስተዳደር ዳይርክተር አቶ አያሌው አቲሳ÷ መንገዶቹ ለአውቶቡስ ብቻ ተብለው የተለዩት ብዙ ሰው ስለሚይዙ የትራፊክ መጨናነቅ ሳያጋጥማቸው ተሳፋሪዎች በሰዓት ወደሚፈልጉበት ቦታ እንዲደርሱ ለማድረግ ነው ብለዋል።
በዚህም በስራ መግቢያ ሰዓት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት እንዲሁም በስራ መውጫ ሰዓት ደግሞ ከ10 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን ተክትሎም መስመሩን እንዲጠቀሙ ያልተፈቀደላቸው 15 ሺህ 506 አሽከርካሪዎች ደንብ በመተላለፍ በገንዘብ መቀጣታቸውን ተናግረዋል።
አውቶቡሶቹ ተለይተው መንገዱን እንዲጠቀሙ መደረጉ ቀደም ሲል የነበራቸው የምልልስ ምጣኔ መጨመሩን ጠቁመዋል።
ለአውቶቡሶቹ የተለየውን መንገድ እንዲጠቀሙ የተፈቀደላቸው የመንግሥት ተሽከርካሪዎች አለመኖራቸውን ጠቅሰው÷ ነገር ግን የአደጋ እና የጸጥታ ስራ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች መንገዱን መጠቀም ይችላሉ ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት ለአውቶቡስ ተብለው የተለዩት መስመሮች 5 መሆናቸውን በመግለጽም ከሜክሲኮ ጀርመን፣ ከሜክሲኮ ስታዲየም፣ ከለገሀር ፒያሳ፣ ከላምበረት አቤም እና ከገርጂ ቶቶት ጎሮ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡
ወደ ፊት እየተጠና እንዲሁም የፍሰት ሁኔታው እየታየ ሌሎች መስመሮች ሊጨመሩ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩንም አቶ አያሌው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።
በመሳፍንት እያዩ