የግብርና ምርት አቅራቢ አርሶ አደሮችን ከሸማቾች ጋር የሚያገናኝ መተግበሪያ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የአርሶ አደሮችን ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ ሁለት መተግበሪያዎችን ይፋ አድርጓል።
መተግበሪያዎቹ ዲጂታል ማርኬት ሊንኬጁ እና አውቶሜሽን ኢንፑት ቮቸር (ኢ_ቮቸር 2.0) የተሰኙ ናቸው።
ዲጂታል ማርኬት ሊንኬጁ የተሰኘው መተግበሪያ አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶችን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ምርት ለሚገዙ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ነው ተብሏል።
መተግበሪያው የአርሶ አደሮችና የግብርና ምርት ሸማቾችን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ የገበያ ዋጋ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚያስችል ተገልጿል።
አርሶ አደሮች ምርታቸውን በተገቢ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እንዲያቀርቡ በማስቻል የዋጋ መረጋጋትን እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል።
መተግበሪያው በ6077 አጭር የጽሑፋ መልዕክት እና በድረ ገጽ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፤ በሳምንት በ311 ገበያዎች የ19 የምርት አይነቶችን 244 ሺህ የገበያ መረጃዎች ተደራሽ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።
አሁን ላይ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን የተመዘገቡ አባላት ያሉት መተግበሪያው፥ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች መረጃ ይሰጣል ተብሏል።
አውቶሜሽን ኢንፑት ቮቸር (ኢ_ቮቸር 2.0) የተሰኘው መተግበሪያ ደግሞ አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶችን በቀጥታ ከአቅራቢዎች ማግኘት የሚያስችላቸው መሆኑ ተገልጿል።
መተግበሪያው አርሶ አደሮች የግብርና ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከአቅራቢዎች እንዲያገኙ ያስችላል ነው የተባለው።