ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ላይ ለውጥ እንዲመጣ በትብብር መስራት ይገባል – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመጣ በጥምረት መስራት ያስፈልጋል ሲሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡
ከተረጂነት ወደ አምራችነት በሚል መሪ ሃሳብ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና የሥራ ፕሮጀክት የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በ2ኛው የፕሮጀክት ምዕራፍ በ88 ከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዜጎችን በቀጥታ ድጋፍ እና በልዩ ድጋፍ ተጠቃሚ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድና በአደጋ ጊዜ ምላሽ እንዲሁም በአከባቢ ልማት ሥራዎች እንዲሳተፉና ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ እንደሚገኝ ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
መድረኩ በ2016 በፌዴራልና በክልሎች የተሰሩ ሥራዎችና በፕሮጀክቱ ሥራ ላይ የተጠኑ ጥናቶችን ለመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱን በማከናወን በተገኘው ውጤታማ አፈጻጸም ፕሮጀክቱ ወደ 88 ከተሞች እንዲስፋፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡
በቤዛዊት ከበደ