የሐረሪ ክልል የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንን ካለበት ደረጃ ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚደረግ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልልን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንን ካለበት ደረጃ ለማሳደግ ብሎም በሳኒቴሽን እና ኢነርጂ ዘርፍ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገለጸ።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ከውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ አቶ ኦርዲን በድሪ እንደገለጹት÷ የክልሉን የመጠጥ ውሃ እጥረት ለመፍታት የአጭር፣ የረጅም እና መካከለኛ ጊዜ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።
እንዲሁም የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እያደረገ የሚገኘውን የሳኒቴሽን እና ኢነርጂ ዘርፍ ድጋፍን እንዳደነቁ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው÷ የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንን ካለበት ደረጃ ለማሳደግ ብሎም በሳኒቴሽን እና ኢነርጂ ዘርፍ ተቋማቸው አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
እንዲሁም የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሐረሪ ክልል ሶፊ ወረዳ 18 ኪሎ ዋት ሀይል የሚያመነጭ የሶላር ፕሮጀክት አስመርቆ አገልግሎት አስጀምሯል፡፡
ፕሮጀክቱ ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ተመላክቷል።