Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤን ለማስተናገድ ስምምነት ተፈራረመች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጋር የዓለም አቀፉን የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ስብሰባ ከሀምሌ 15 እስከ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ለማስተናገድ የአስተናጋጅ ሀገር ስምምነት ተፈራረመች።

ስምምነቱን በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ እና የተመድ የምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሃፊ ሊ ጁንዋ ፈርመዋል።

አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ÷ ኢትዮጵያ ስብሰባውን ማስተናገዷ የተመድ አሰራርን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እና የባለብዙ ወገን ትብብሮች እንዲጠናከሩ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክትል ዋና ጸሃፊዋ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ስብሰባውን ለማስተናገድ ያላትን ቁርጠኝነት እና ሚና አድንቀው ሁለቱ ወገኖች ለዘላቂ ልማት ግቦች አጀንዳ ማስፈጸሚያ ፋይናንስ ለማሰባሰብ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማነሳሳት ጉባዔው ያለውን ጠቀሜታ አውስተዋል።

ኢትዮጵያ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሦስተኛውን የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ ማስተናገዷ ይታወሳል፡፡

ከመጭው ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ስብሰባ የአዲስ አበባ የድርጊት መርሃ ግብርን አፈፃፀም እንደሚገመገም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ የመላክታል፡፡

እንዲሁም በቀጣይ ዓመት በስፔን ለሚካሄደው አራተኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.