የኢትዮ- ጣሊያን የቢዝነስ ፎረም መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ- ጣሊያን የቢዝነስ ፎረም በጣሊያን ሚላን ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በፎረሙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ÷ ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በፖለቲካ፣ በኢንቨስትመንት እና በንግድ ዘርፍ ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል፡፡
በሀገራቱ መካከል በኢኮኖሚው መስክ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከርና ማስፋት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
መሰል የቢዘነስ ፎረሞች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ሚናቸው የላቀ መሆኑን በመግለጽ ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚወስኑ ኩባንያዎች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በሮም የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳ በበኩላቸው ÷ ጣሊያናውያን ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የማቴይ ፕላን ግብረ ኃይል አባል ሎሬንዞ ኦርታና፣ የፋይናስ ተቋም የሆነው የሲ.ዲ.ፒ ተወካይ ማርቲና ማዲዮ እንዲሁም በሮም በቦንኤልኤረዲ የህግ አማካሪ ሚካኤል ስፖናሮ ÷ የጣሊያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የሚሰጡ ድጋፎችና ምቹ ሁኔታዎችን አስመልክተው ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።
በፎረሙ የተፈጠረውን ዕድል በመጠቀም የሁለቱ ሀገራት ኩባንያዎች በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት በመፈራረም ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚገቡ ይሆናልም መባሉን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡