አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የመፍትሔዎች ማሰቢያ መንገድ ሆኗል- ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የመፍትሄዎች መሳሪያ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔዎች ማሰቢያ መንገድም ሆኗል ሲሉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኤ.አይ ሠመር ካምፕ 2024 የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ ሰልጣኞችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በዚህ ወቅት በየዓመቱ የመደበኛ ትምህርት ሲጠናቀቅ ኢንስቲትዩቱ ሰልጣኞችን ተቀብሎ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዙሪያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ማሰልጠኑን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ችግር ፈቺ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የፈጠራ ባለቤት እንዲሆኑ ኢንስቲትዩቱ በስልጠናው አቅም እንደሚፈጥርላቸውም ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ለሦስተኛ ጊዜ በሚሰጠው ይህ ስልጠና 200 ሰልጣኞችን በመቀበል ለማሰልጠን ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡