አዘርባጃን ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ ትሰራለች-ፕሬዚዳንት ኢሃም አሊዬቭ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዘርባጃን ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ እንደምትሰራ ፕሬዚዳንት ኢሃም አሊዬቭ ገለጹ።
ሁለተኛው የሹሻ ዓለም ዓቀፍ የሚዲያ ፎረም በአዘርባጃን መካሄድ ጀምሯል።
“የሃሰተኛ ትርክትን ማጋለጥ፤ የሃሰተኛ መረጃን መዋጋት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ በሚገኘው ፎረም ላይ ከ50 ሀገራት የተወጣጡ ከ150 በላይ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች፣ ጋዜጠኞችና ምሁራን እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ከፎረሙ ተሳታፊዎች ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ፕሬዚዳንቱ÷ሀገራቸው ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ በኢትዮጵያ ኤምባሲ በመክፈት የጀመረችውን ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።
ፕሬዚዳንቱ በቀጣናዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ጉዳዮች ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ወቅቱ ከፍተኛ የሆነ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ያለበት በመሆኑ የመገናኛ ብዙሃንና ባለሙያዎች በጥንቃቄ መስራት ይገባቸዋል ተብሏል።
በፎረሙ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት የደረሰበትን ደረጃ መገንዘብ፣ ሃሰተኛ መረጃዎችን መቋቋም የሚችል ማህበረሰብ መፍጠር፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመገናኛ ብዙሃን እና በሃሰተኛ መረጃ ስርጭት የሚያመጣው ለውጥና የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄና የመገናኛ ብዙሃን ሚና በሚሉ ርዕሶች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።
በምስክር ስናፍቅ