ፕሬዚዳንት ትራምፕ በልጅነታቸው አሜሪካ ገብተው ያለ ህጋዊ ሰነድ ለሚኖሩ ስደተኞች ከለላ የሚሰጠው ፕሮግራም እንዲቋረጥ ያቀረቡት እቅድ ውድቅ ሆነ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በልጅነታቸው አሜሪካ ገብተው ያለ ህጋዊ ሰነድ ለሚኖሩ ስደተኞች ከለላ የሚሰጠው ፕሮግራም እንዲቋረጥ ያቀረቡትን እቅድ ውድቅ አደረገ።
ፕሮግራሙ በፈረንጆቹ 2012 በይፋ የተጀመረ ሲሆን፥ ሌላ ሃገር ተወልደው በልጅነታቸው አሜሪካ የገቡና ለመኖር የሚያስፈልገውን ህጋዊ ሰነድ ለማያሟሉ ስደተኞች ከአሜሪካ እንዳይወጡ ከለላ የሚሰጥ ነው።
በዚህ ፕሮፐግራም መሰረት ስደተኞች በአሜሪካ መስራት እንዲችሉ የሚያደርግ የሁለት አመት የቆይታ ጊዜ እድሳት ይደረግላቸዋል።
ይህ በቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የተጀመረው ፕሮግራም ለስደተኞች ዜግነት መስጠትን ግን አያካትትም።
አሁን ላይም ፕሮግራሙ ከለላ የሚሰጣቸው ወደ 650 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፥ ትራምፕ የስደተኞቹ የአሜሪካ ቆይታ እንዲያበቃ እቅድ አቅርበው ውድቅ ተደርጎባቸዋል።
የአሁኑ የፍርድ ቤት ውሳኔ ግን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ፕሮግራሙን ለማስቆም ከሚያደርጉት ተጨማሪ ጥረት አያስቆማቸውም ተብሏል።
ትራምፕም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አስደንጋጭ እና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው በሚል አጣጥለውታል።
በአንጻሩ ደግሞ ለፕሮግራሙ ፖለቲካዊ ሳይሆን ህጋዊ መፍትሄ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚያስፈልገውን ሂደት እንጀምራለን ሲሉም ተደምጠዋል።
ምንጭ፦ ሬውተርስ