Fana: At a Speed of Life!

ከክረምቱ ጋር በተያያዘ ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መንግሥት አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከክረምቱ ጋር በተያያዘ ለመሬት መንሸራተት፣ ውኃ ሙላት እና መሰል አደጋዎች ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢፌዴሪ መንግሥት አሳሰበ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እስከ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች ከክረምቱ ጋር በተያያዘ በደረሱ አደጋዎች ሳቢያ ለተጎዱ ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ÷ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ተመኝቷል፡፡

በጉዳዩ ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው የጥንቃቄ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የጥንቃቄ መልዕክት!

ከክረምቱ ዝናብ ጋር ተያይዞ በአንድ አንድ የሃገራችን አካባቢዎች በደረሱ የመሬት መንሸራተትና የዉሃ ሙሌት ምክንያት የበርካታ ዜጎቻችን ሕይወት አልፏል፤ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም አደጋም ደርሷል፡፡

በትናንትናው ምሽት በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ወንሾ ወረዳ ግሽሬ ጉዱ ሞና ሆሞ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የ6 (ስድስት) ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም አደጋም ደርሷል፡፡

በተጨማሪም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስሃላ ሰየምት ወረዳ ወደ ዝቋላ ወረዳ በተከዜ ወንዝ በጀልባ ሲጓዙ በነበሩት ሰዎች ላይ በውሃ ሙሌት ምክንያት በደረሰው አደጋ የሰው ሕይወት አልፏል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በደረሱ አደጋዎች ሳቢያ ለተጎዱ ዜጎች የተሰማዉን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻል፡፡ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡

ህብረተሰቡ ወቅቱ የክረምት ወቅት መሆኑን በመገንዘብ ለመሰል አደጋዎች ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያድርጉ መንግሥት ያሳስባል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.