ገጠሩን ብቻ ሳይሆን ከተሞችንም አረንጓዴ ያለበስንበት አረንጓዴ ዐሻራ ዓለም አቀፍ መለያችን ሆኗል- ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ገጠሩን ብቻ ሳይሆን ከተሞችንም አረንጓዴ ያለበስንበት አረንጓዴ ዐሻራ ዓለም አቀፍ መለያችን ሆኗል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በቢሾፍቱ ከተማ ቱሉ ፎቃ ተራራ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ በስኬት ያስቀጠለችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኘንበት ነው ያሉት አቶ ተመስገን÷ ገጠሩን ብቻ ሳይሆን ከተሞችንም አረንጓዴ ያደረግንበት መገለጫችን ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ችግኝ ተከላ የተከናወነበት ቦታ ታሪካዊና የቢሾፍቱ ከተማ መተንፈሻ መሆኑን ጠቅሰው÷ አካባቢውን ተጨማሪ የጉብኝት መዳረሻ ለማድረግ ሰፊ ዕድል እንዳለም አመላክተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው÷ የተተከሉ ችግኞችን ተከታትሎ በማጽደቅና የቢሾፍቱ ከተማን በማስዋብ ተግባር ላይ ሁሉም በኃላፊነት እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡
በፍሬሕይወት ሰፊው