ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የግንባታ ሒደትን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የግንባታ ሒደትን ጎብኝተዋል፡፡
ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ፣ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ እና የፌደራልና የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል።
አመራሮቹ የስታዲየሙን የግንባታ ሂደት የጎበኙ ሲሆን÷ በክልሉ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
ሁለተኛ ዙር ግንባታው በ2015 ዓ.ም ታህሳስ ወር የተጀመረው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በመገንባት ላይ ሲሆን ግንባታው 57 በመቶ ደርሷል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን (ካፍ) የመመዘኛ መስፈርት ባሟላ መልኩ እየተገነባ የሚገኘው ስታዲየሙ፤ 47 በሚሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ የተለያየ ዘርፍ ኮንትራክተሮች እየተገነባ ይገኛል።
ደረጃቸውን የጠበቁ ወንበሮች የማምረት ስራው በውጭ ሀገር እየተከናወነ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን÷ ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ በተዘጋጀውና በሚነጠፈው ሳር፣ በወንበሮቹና የልዩ መስተንግዶ መቀመጫዎች ለየት እንደሚያደርገው ተገልጿል።
ግንባታውን በ2017 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ስራው በመከናወን ላይ ይገኛል ተብሏል።
ጉብኝት ያደረጉት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎቹ በስታዲየሙ ዙሪያ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነዋል።
በፍሬህይወት ሰፊው