Fana: At a Speed of Life!

የቴሌኮም ገመድ በመስረቅና የተሰረቀውን ንብረት በመቀበል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለህዝብ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ የቴሌኮም ገመድ በመስረቅ የተጠረጠረ አንድ ግለሰብና የተሰረቀውን ንብረት በመቀበል የተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበበ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን ፈፅመዋል የተባለው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ካራ ቆሬ አካባቢ ሲሆን÷ አንደኛው ተጠርጣሪ ጨለማን ተገን አድርጎ የኢትዮ ቴሌኮ ንብረት የሆነውን ገመድ በመቁረጥ ይዞ ሲሄድ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተመላክቷል።

 

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በተደረገ ምርመራ ሌሎች ለወንጀሉ ተባባሪ የሆኑ በተለይም በተቀባይነት ከወንጀሉ ጋር ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

ግለሰቦቹ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አካባቢ የተሰረቀ የኤሌክትሪክ ገመድ የሚቀበሉ ስለመሆናቸውም ታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅትም ከ1 ሺህ ሜትር በላይ የሚሆን የኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ንብረት የሆነ ገመድ ከነመቁረጫቸው ተይዟል ነው የተባለው፡፡

የተሰረቁ የኢትዮ ቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ገመድን ከሚቀበሉ ግለሰቦች ቤት ውስጥ 3 ጀነሬተሮች፣ 4 የሃይል ማስነሻ ባትሪ እና ባለሙያዎች ለስራ የሚጠቀሙባቸውን ቀበቶዎች መያዛቸውን ተገልጿል፡፡

በተጠርጣሪዎቹ ላይ አስፈላጊው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.