በእሳት አደጋ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ ሁለት ሰዎች ተጎዱ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቡልቡላ ማርያም ማዞሪያ አካባቢ በተነሳ የእሳት አደጋ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ በሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ፡፡
አደጋው የተከሰተው በመኪና ዕቃ መለዋወጫ ሱቅ ውስጥ መሆኑን እና በሱቁ ውስጥ ተቀጥራ የምትሠራ የ20 ዓመት ወጣት ሕይወቷ ማለፉን የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ሁለት ሰዎች በጭስ የመታፈን ጉዳት እንደደረሰባቸውም ነው ያረጋገጡት፡፡
የኮሚሽኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሁለቱን ሰዎች ከአደጋው ማትረፍ መቻላቸውን ጠቅሰው የእሳት አደጋው ተስፋፍቶ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር ችለዋል ነው ያሉት፡፡
በሱቁ ውስጥ በጀሪካንና በላስቲክ ጠርሙሶች የነበረ ነዳጅ ለእሳቱ በፍጥነት መስፋፋት ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡
የነዳጅ ሽያጭም ሆነ ክምችት መከናወን ያለበት በተፈቀደለት የነዳጅ ማደያ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡