የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ትግበራ የተፋሰሱ ህዝቦች ትልቅ ተስፋ የሚያደርጉበት ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዩጋንዳ ካምፓላ 32ኛው የናይል ተፋሰስ ሀገራት የሚኒስትሮች ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)÷ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ ስምምነት ትግበራ ተከትሎ የሚመጣው የናይል ቤዝን ኮሚሽን ምስረታ የተፋሰሱ ህዝቦች ትልቅ ተስፋ እንደሰነቁበት ተናግረዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት በናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የታየው አዎንታዊ እመርታ ከመቼውም ጊዜ በላይ የናይል ቤዚን ኮሚሽንን ለማቋቋም ወሳኝ ምእራፍ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ ለናይል ቴክኒክ ኮሚቴና ለናይል ቤዝን ኢኒሸቲቭ ተቋማዊ የትግበራ እቅድ ለማዘጋጀት አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ሚኒስትሩ የናይል ቤዝን ኢኒሼቲቭ ሀብት ከማሰባሰብ ጋር ተግዳሮቶችና እጥረቶች እንዳሉበት አንስተው፤ በጉባኤው አስቻይ ሁኔታዎችን የሚፈጥር አቅጣጫ እንደሚቀመጥ እምነታቸውን መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከ32ኛው የናይል ሀገራት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባኤ ጎን ለጎን 27ኛው የናይል ኢኳቶሪያል ሀይቆች ካውንስል ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።