በአዲስ አበባና ር ጃው ከተማ መካከል የእህትማማችነት ግንኙነት ለመመስረት ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ‹አዲስ አበባ እና የቻይናዋ ር ጃው ከተማ የእህትማማችነት ግንኙነት ለመመስረት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ እና የር ጃው ከተማ ምክትል ከንቲባ ዣንግ ዲአንሁ ፈርመዋል።
አቶ ጃንጥራር አባይ የር ጃው ከተማ ያላት ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ፣ የከተማ ፕላን እና የኢኮኖሚ እድገት ስኬት ተነሳሽነትን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማዋ ለአረንጓዴ ልማትና ኢኖቬሽን ያላት ቁርጠኝነት አዲስ አበባ ካላት ራዕይ ጋር ትስስር እንዳለው ገልጸው፤ ምርጥ ተሞክሮን ለመማር እና ለሁለቱም ከተሞች በሚጠቅሙ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለ ጠቁመዋል።
በከተሞቹ መካከል የእህትማማችነት ግንኙነት ለመፍጠር የተደረሰው ስምምነት በዘላቂ ልማት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በባህል፣ በንግድ፣ በትምህርት እና ጤና መስኮች በትብብር በመስራት የጋራ ብልጽግና እና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ እምነታቸውን ገልጸዋል።
የር ጃው ከተማ ምክትል ከንቲባ ዣንግ ዲአንሁ በበኩላቸው፤ በር ጃው ከተማ የሚገኙ አምራች ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ የንግድ አጋሮቻቸው ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል።
የመግባቢያ ስምምነት ሁለቱ ከተሞች በተለያዩ መስኮች የሚኖራቸውን ትብብር ያጠናክራል ማለታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።