ምክክር ኮሚሽኑ ከነገ በስቲያ በሐረሪ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ ይጀመራል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሐረሪ ክልል ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም አጀንዳ ማሰባሰብ እንደሚጀምር ተገለፀ፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሀመድ ድሪር÷ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በየወረዳው ከሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን አስመርጦ ማዘጋጀቱን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ኮሚሽኑ ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ በሀረሪ ክልል በሚከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ የማህበረሰብ ወኪሎች፣ የክልሉ የመንግስት አካላት ፓርቲዎች፣ የሶስቱ የመንግስት አካላት ተወካዮች፣ የተለያዩ ተቋማት እና ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ታዋቂ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደሚሳተፉና የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን የሚያዘጋጁበት ሂደት እንደሆነ ገልፀዋል።
የክልሉ ነዋሪዎች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በንቃት እንዲሳተፋ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ተገኘወርቅ ጌቱ (ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክክሩ እጅግ መሰረታዊ የሆኑ ሀሳቦችን ለመውሰድና አንኳር ጉዳዮችን ለመለየት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
በዚህ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ 1 ሺህ ዜጎች የሚሳተፉ ሲሆን÷ ለስድስት ቀናት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል፡፡
በፈቲያ አብደላ