ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር እንደምትሰራ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ እንደምትሰራ በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኡሪያት ቻም ኡጋላ ገለጹ፡፡
በአምባሳደሩ ከቲቪ ብሪክስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፥ የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ስላለው ጥቅምና ተያያዥ ጉዳዮች አንስተው አብራርተዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት በተለያዩ ባለብዙ ወገን ግንኙነት ተሳትፎ እንደነበራትና እንዳላት አንስተው፤ ከዚህም መካከል አንዱ ብሪክስን መቀላቀሏ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከብሪክስ ሀገራት ጋር ያላት የባለብዙ ወገን ግንኙነት ቀደም ሲል ጀምሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
የዓለምን ከ14 በመቶ በላይ ህዝብ የያዙት የብሪክስ አባል ሀገራት በኢኮኖሚ በፍጥነት እያደጉ ያሉ ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደጉ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ተርታ የምትጠቀስ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በዚሁ የባለብዙ ወገን የምታደርገው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ብሪክስ አብሮ ማደግን እና የሀገራትን ሉዓላዊነት ማክበርን የሚሰብክ ቡድን መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ብዝሃነት እንዲኖርና ዓለም ለሰው ልጆች የተሻለች ስፍራ እንድትሆን የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በመሆን በዚህ ጉዳይ የራሷን ጥረት ታደርጋለች ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ግብርናዋን ለማዘመን፣ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋት፣ የኃይል አቅርቦቷን ለማሳደግ፣ ለመሰረተ-ልማት እድገት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይ ሲቲ) እና ሳይበር ደህንነት ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በሰፊው መስራት እንደሚያስችላትም ጠቁመዋል፡፡