Fana: At a Speed of Life!

የበለጸገ ማኅበረሰብ መፍጠርን ተግባር ተኮር ተልዕኮ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተመጣጠነ ምግብን የሚያገኝና የበለጸገ ማኅበረሰብን መፍጠር ቀዳሚና ተግባር ተኮር ተልዕኳችን አድርገን መሥራት አለብን ሲሉ የክልል ርዕሳነ-መሥተዳድሮችና ሚኒስትሮች ገለጹ።

በ2022 ዓ.ም መቀንጨርን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ግብ ተይዞ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን፥ ይህን ለማሳካት በ2016 በጀት ዓመት የተተገበሩ የምግብና የሥርዓተ-ምግብ አፈጻጸሞች ተገምግመዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ፥ በቂ የምግብ ሥርዓት እንዲኖርና ትውልዱ ብቁ ሆኖ እንዲያድግ ተግባር ተኮር አመራር የመስጠት ግዴታችንን መወጣት ይጠበቅብናል በማለት ገልጸው፤ የሥርዓተ-ምግብ ግብን የማረጋገጥና የበለፀገ ማኅበረሰብ የመፍጠር ጉዳይ ለአንድ አካል የሚተው አለመሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፥ ምግብን በስፋት ከማምረት ባለፈ ሕብረተሰቡ ጥራቱ የተጠበቀና ስብጥር ያለው ዓይነተ-ብዙ ምግብን እንዲጠቀም በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ኢኒሼቲቮችን ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የሰቆጣ ቃል ኪዳን ዋናው ግብ የሚሳካው መቀንጨርና መቀጨጭን ሙሉ ለሙሉ ማስቆም ሲቻል ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ናቸው፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን፥ ጤናማና የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር፣ በስንዴ ልማት፣ በአረጓዴ ዐሻራና በሌማት ትሩፋት እየተተገበሩ ያሉ ኢኒሼቲቮች ከሥርዓተ-ምግብነት ትልምች ጋር ስለሚተሳሰሩ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፥ ትውልዱ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ የምርት ቅንጅትና ማቀነባበርን መፍጠር፣ ምግብን ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ ማጓጓዝ አስፈላጊ ስለሆነ ለሎጅስቲክስ ዘርፉ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፥ ከታች ዕድሜ ጀምሮ ስለ ሥርዓተ-ምግብና የተመጣጠነ ምግብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖር አዳዲስ የማስተማሪያ ዘዴዎችን ለመተግበር መታሰቡን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የማይበገርና ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር የተናበበ የምግብ ሥርዓትን ለመተግበር ግልፅ ዕቅድ አውጥታ እየሠራች መሆኗን የገለጹት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፥ በመንግሥት መዋቅር በኩል እኩል ያለመፈጸም ችግር አለ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የመቀንጨር ችግር አሁንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፥ ትውልድን በተሟላ ዕድገት ለመገንባት ትኩረት ይፈልጋል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የግብርና ምርታማነት ቢጨምርም፥ የአመጋገብ ባህልና ሥርዓታችን ደካማ መሆኑ ሕጻናት የተመጣጠነ ምግብ እንዳያገኙ አድርጓል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.