Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ከተሞች ፎረምን በስኬት ለማስተናገድ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የመጀመሪያውን የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በስኬት ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ፎረሙ “ዘላቂ የክትመት ምጣኔ ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063” በሚል መሪ ሃሳብ ነው ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄደው፡፡

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ዴዔታ ፋንታ ደጀን እንደገለጹት÷ፎረሙ አፍሪካዊ ወንድማማችነትን ከማጠናከር ባለፈ አህጉሪቷ ዘመናዊ ከተሞችን ለመገንባት የሚያስችላት ምክክር የሚደረግበት ነው፡፡

ኢትዮጵያም ፎረሙን በስኬት ለማስተናገድ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚመራ ብሔራዊ እና የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም የቅደመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

በፎረሙ ከአፍሪካ ሀገራት በተጨማሪ በሌሎች አህጉር ያሉ ከተሞች እንደሚሳተፉ ገልጸው÷የሀገር መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ተመራማሪዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚታደሙ ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካን አጀንዳ 2063 ላይ መሠረት ያደረጉ የልማት ግቦች፣ ከተሞችን የተመለከቱ የተለያዩ ጉዳዮችና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ላይ ውይይት የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከተሞች ያላቸውን ልምድ የሚያካፍሉበት ኤግዚቢሽን መዘጋጀቱን አንስተው÷የሀገር መሪዎችና ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት የጎንዮሽ ውይይቶች እንደሚካሄዱም ጠቅሰዋል፡፡

ሆቴሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የጸጥታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ለኢዜአ ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡ እንግዳ የመቀበል ባህላችንን አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ በፎረሙ ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን እንዲቀበል ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.