በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚከናወኑ ተግባራት ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፉ ናቸው – ቢልለኔ ስዩም
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚከናወኑ ተግባራት ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፉ ሥራዎች መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጥሪ ተከትሎ በፓሪስ ኦሊምፒክ የድል ባለቤት የሆኑ አትሌቶችን ጨምሮ አርቲስቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል ዛሬ ችግኝ ተክለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ አረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ሥጋትን ከመከላከል አንጻር የማይተካ ሚና ይጫወታል።
የአረንጓዴ አሻራ ተግባራት የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባሻገርም ጽዱ፣ ውብና ጤናማ አካባቢን ለትውልድ ለማስተላለፍ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለመጨመር ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ የተሳተፉ ዜጎች የትልቅ ታሪክ አካል ናቸው ሲሉም ጠቁመዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግች በመትከልና በመንከባከብ የሚከናወኑ ተግባራት ለትውልድ መሥራት መሆኑን አስረድተው፤ ሁሉም ኅብረተሰብ የአረንጓዴ አሻራውን በማሻረፍ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የተሳተፈው አትሌት ታምራት ቶላ÷ በድሉ ማግስት የአረንጓዴ አሻራውን በማሳረፉ መደሰቱን ተናግሯል።
ችግኞችን መትከል አትሌቶች የልምምድ መርሐ ግብራቸውን አረንጓዴ የተላበሰ ሥፍራ ላይ ለማከናወንም ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ጠቁመው÷ ንጹህ አየር ለማግኘት እንደሚረዳ ገልጿል።