ግብፅ አሁንም እንዲከበርላት የምትሻው የቅኝ ግዛት ዘመን የአባይ ውሃ ድርሻ ክፍፍል ምን ይመስላል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረመውን የውሃ ድርሻዬን ይቀንስብኛል በሚል በመቃወም ላይ ትገኛለች።
ግብፅ አሁንም እንዲከበርላት የምትሻው የቅኝ ግዛት ዘመን የአባይ ውሃ ድርሻ ክፍፍል ስምምነት በብሪታኒያ አመቻችነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1929 የተፈረመ ነው።
ስምምነቱም በግብፅ እና በብሪታንያ መካከል የተካሄደ ሲሆን፥ በወቅቱም ብሪታኒያ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ እና ሱዳንን በመወከል ነው ስምምነቱን የፈረመችው።
ስምምነቱም በወንዙ ላይ ለግብፅ ሙሉ የመጠቀም መብት የሚሰጥ ሲሆን፥ በላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚገነቡ እና የግብፅን የውሃ ድርሻ የሚጎዱ ማንኛውም የግድብ እና የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ ውሳኔ የማሳለፍ ሙሉ ስልጣን የሰጣት ነበር።
በመቀጠልም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1959 ላይ ግብፅ እና ሱዳን የመጀመሪያውን ስምምነት መነሻ በማድረግ አዲስ ስምምነት ይፈራረማሉ።
በውሃ ድርሻ ክፍፍል ስምምነቱ መሰረትም፦
– በዓመት 55 ነጥብ 5 ቢሊየን ክዩቢክ ሜትር ውሃ ማለትም 66 በመቶ ለግብፅ
– በዓመት 18 ነጥብ 5 ቢሊየን ክዩቢክ ሜትር ውሃ ማለትም 22 በመቶ ለሱዳን
– በዓመት 84 ቢሊየን ክዩቢክ ሜትር ውሃ 12 በመቶ በትነት መልክ የሚባክን ነው
ሀገራቱ ይህንን ስምምነት በሚፈራረሙበት 86 በመቶ የአባይ ውሃ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያን ያላማከሩ መሆኑን በወቅቱ የተፈረሙ ስምምነቶች ያመላክታሉ።
ታዲያ ለመስማማት እንድንችል የፈለግነውን ስጡን የሚሉት ግብፆች፤ ወቅቱ ኢትዮጵያን ሳያማክር የተፈረመው ስምምነት አሁንም እንዲከበርላት አጥብቃ እንደምትሻ በተለያዩ ድርድሮች ላይ ያሳየቻቸው አቋሞች ያመላክታሉ።
ግብፅ የህዳሴ ድግብ ውሃ መያዝ ሲጀምር ጉዳት እንደሚያደርስባት በማስመሰል ማደናገሪያዎችን ጭምር እያቀረበች ቢሆንም፥ ኢትዮጵያ ግን በግድቡ ዙሪያ ግልፅነትን ለመፍጠር በሯን ለድርድር ክፍት ካደረገች ውላ አድራለች።