በአማራ ክልል በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር ለሚከናወነው ችግኝ ተከላ ዝግጅት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር ለሚከናወነው አረንጓዴ ዐሻራ የማኖር መርሐ-ግብር የአማራ ክልል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
በዚሁ መሠረት ችግኝ ተከላ የሚከናወንባቸውን ሥፍራዎችን ጨምሮ የችግኝ ዓይነቶችን እና ብዛት የመለየት ሥራ መጠናቀቁን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በመርሐ-ግብሩም በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ እና የግብርና ባለሙያዎችም ክትትል እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በተለያዩ አካባቢዎች የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ይታወቃል፡፡