ሰራተኞች በክህሎታቸው ተመዝነው የሚያገለግሉበት አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል – ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የመንግስት ሰራተኞች በዕውቀታቸውና ባላቸው ክህሎት ተመዝነው የሚያገለግሉበት አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
በክልሉ የመንግስት ሰራተኞች አፈፃፀም ምዘና ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
ወ/ሮ አለሚቱ በዚህ ወቅት÷ በክልሉ ሰራተኛው ለተመደበበት የሥራ መደብ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ የማጣራት ሥራዎች መጠናከር አለባቸው ብለዋል።
የትኛውም ሰራተኛ በትምህርት ዝግጅቱና ክህሎቱ የሚያገለግልበት አሰራር ደንብና መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ ተግባራዊ እንደሚደረግም አስረድተዋል።
የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር ጋትሏክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ስራን በውጤታማነት ለመምራት የሚያስችል የአፈጻጸም አመራር ስርዓት በመዘርጋት ሁሉም ሰራተኛ በተቀመጠው የምዘና መስፈርት መመዘን አለበት ብለዋል፡፡
በየትኛውም ተቋም ሰራተኛ መቀጠር ያለበት ባለው የትምህርት ዝግጅትና ልምድ እንዲሁም ለሚመደብበት ቦታ በቂ ክህሎት መኖሩ ሲረጋገጥ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ኛሞች ጊል÷ ሀገሪቱ የያዘችውን የዕድገት ለውጥ እንቅስቃሴ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር የሰራተኛውን አቅምና ክህሎት ማሳደግ እንደሚገባ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡