Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ሁሌም ዝግጁ ናት- አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ሁሌም ዝግጁ መሆኗን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልፅግናፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሰላም እና አንድነት ለማረጋገጥ የውድ ልጆቿን ደም ጭምር በመገበር ገደብ የለሽ አጋርነቷን አሳይታለች ብለዋል፡፡

አቶ አደም ፋራህ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል አንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ሁላችንም እንደምንገዘበው ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወደ 1700 ኪ.ሜ የሚጠጋ በድንበር የሚዋሰኑ እና ተመሳሳይ ባህል፣ ቋንቋ እና ኃይማኖት የሚጋሩ ሕዝቦች ያሏቸው ሀገራት ናቸው፡፡

ይህ በታሪክም ሆነ በዘመናት መሀከል በሚፈጠሩ ትርክቶች ሊቀየር የማይችል እውነት እንደሆነ የምታምነው ሀገራችን፤ ለእድገቷ እና ለብልጽግና ጉዞዋ የሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት እጅጉን ጠቃሚ እንደሆነ በመረዳት በአብሮ ማደግ እሳቤ ሀገረ ሶማሊያ ተጠናክራ እንድትቆም በርካታ ጥረቶችን ስታደርግ ኖራለች፡፡

እ.ኤ.አ 1991 ዓ.ም ከሶማሊያ መንግስት መፍረስ በኋላ ሶማሊያ ዳግም ወደ ሰላም እንድትመጣ ለማድረግ እና የሀገረ መንግስት ህልውናዋ ተረጋግጦ በሁለት እግሯ መቆም እንድትችል በወንድማዊ አጋርነት ኢትዮጵያ በርካታ ጥረቶችን ስታደርግ ኖራለች፡፡

በተለይም በሶማሊያ ከተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነቱ ማግስት የተሰደዱ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እና መጠለያ እንዲያገኙ በማድረግ፣ የሶማሊያን መንግስታዊ ህልውና መልሶ ለማጠናከር የሚደረጉ ውይይቶችን በማመቻቸት፣ በማስተባበርና በመደገፍ ያላሰለሰ ጥረቶችን ስታደርግ እንደኖረች ዘመን የማይሽረው ሀቅ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከፖለቲካዊ ጥረቶች በዘለለ ሀገራችን ኢትዮጵያ የሶማሊያ ሰላም እና አንድነት ለማረጋገጥ የውድ ልጆቿን ደም ጭምር በመገበር ገደብ የለሽ አጋርነቷን አሳይታለች፡፡

ሌላው ሊታወቅ የሚገባው እውነት የሶማሊ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሕዝብ ሀገራችን በሚትከተለው ህብረብሔራዊ ፌደራል ስርዓት ከሌሎች ወንድም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ፍትሓዊ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶቹና ጥቅሞቹ ተከብሮ ለሁሉም ኢትጵያዊያን የምትምች ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በኀብር ሀገሩን እየገነባ የሚገኝ መሆኑ ነው።

እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ በቅርብ ጊዜያት በሀገረ ሶማሊያ ፕሬዚዳንት እየተሰጡ ያሉ መግለጫዎች እና ንግግሮች እጅግ ከእውነታው የራቁ፣ የሁለቱን ሕዝቦች የትስስር ታሪክ የማይመጥኑ፣ መሬት ላይ ያለውን ሀቅ የሚክዱ፣ የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች መልካም ጉርብትና የጋራ ጥቅም ጋር የሚፃረሩ እንደሆነ ለመታዘብ ችለናል፡፡

ሁሌም ቢሆን ኃላፊነት ከሚሰማቸው ፖለቲከኞች የሚነገሩ ንግግሮች ለቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ፍትሓዊና ዘላቂ ጥቅም የሚመጥኑ፣ የወንድማማችነት እና እህትማማችነት ትስስር የሚያጠናክሩ እና የሶማሌ ህዝብ ዋነኛ ተዋናይ የሆነበት የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት የሚጠቅሙ መሆን አለባቸው፡፡

የሶማሊያ ልሂቃን እና መላው ሕዝብም ቀጣይ እጣ ፈንታቸው በከፍተኛ ደረጃ የተቆራኘውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያሻክሩ እንዲሁም የቀጣናውን ሕዝቦች ዘላቂ ጥቅሞች የሚፃረሩ አካሄዶች እና ንግግሮች እንዲቆሙ የድርሻችሁን እንድትወጡ አደራ ማለት እፈልጋለሁ።

የኢትዮጵያ መንግስትም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለጋራ ተጠቃሚነት፣ ለመልካም ጉርብትናና ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት አዎንታዊ ሚናውን አጠናክሮ ለመቀጠልና ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.