ሚሌ የቁም እንስሳት ማቆያ ማዕከል ወደ መደበኛ ሥራ ገባ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውና በአፋር ክልል ሚሌ ከተማ የሚገኘው የቁም እንስሳት ማቆያ ማዕከል (ኳራንቲይን) ወደ መደበኛ ሥራ ገባ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ እና የግብርና ኢንቨስትመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ሚሌ የቁም እንስሳት ማቆያ ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ማዕከሉ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ኢትዮጵያ በራሷ ስም የእንስሳት ሃብቷን ወደ ውጭ እየላከች መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ የማስፋፊያ ሥራ እተከናወነለት መሆኑን እና በአንድ ጊዜም ከ400 ሺህ በላይ የቁም እንስሳትን የማቆየት አቅም እንዳለው አስረድተዋል፡፡
አምባሳደር ድሪባ በበኩላቸው ማዕከሉ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ መገንባቱን ገልጸው÷ በበጀት ዓመቱ 256 ሺህ የቁም እንስሳት ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ 18 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
የማዕከሉን ውጤታማነት ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ አወል አርባ÷ ሕገ-ወጥ የእንስሳት ንግድን የመከላከል ሥራ ትኩረት እንደተሰጠው አስገንዝበዋል፡፡
በመራኦል ከድር