የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የደን ምንጣሮ ስራ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ የሚተኛበት ስፍራ ደን ምንጣሮ ስራ ትናንት ተጀመረ፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም እንደገለፁት፤ ክልሉ በኢንተርፕራይዞች አማካኝነት የሚመነጠር 1 ሺህ ሔክታር መሬት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ተረክቦ ትናንት የምንጣሮ ስራው እንዲጀመር አድርጓል ።
በመጭው ሐምሌ ወር ውሃ ለመሙላት የተያዘውን እቅድ እንዲሳካ ከወዲሁ የደን ምንጣሮ ስራውን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ 2 ሺህ አባላት የያዙ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ኤጀንሲው የምንጣሮ ስራውን በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወን የቅርብ ክትትል ያደርጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የጤና፣ የጸጥታ እና ሌሎችም ቡድኖች ምንጣሮውን ከሚያካሂዱ ኢንተርፕራይዞች ጋር አብረው ወደ ስፍራው ገብተዋል ብለዋል፡፡
ለስራው የሚያስፈልግ በጀት እና ሌሎች ግብአቶች ለኢንተርፕራይዞቹ መቅረቡን መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል ።
አጠቃላይ ለምንጣሮ ስራው 32 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በላይ በጀት እንደተያዘለትም ከዋና ዳሬክተሩ ገለጻ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በደን ምንጣሮ ስራው መሳተፍ የጀመሩ ኢንተርፕራይዞች በበኩላቸው ስራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቀው ለማስረከብ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል ።