Fana: At a Speed of Life!

አርጎባ ልዩ ወረዳ ከነበረበት ድርቅ አገግሞ የተሻለ ምርት ማግኘት የሚችለበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የአርጎባ ልዩ ወረዳ ከነበረበት ድርቅ አገግሞ በ2016/17 የምርት ዘመን የተሻለ ምርት ማግኘት የሚችለበት ሁኔታ ላይ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡

ባለፈው ዓመት ከ157 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ ቢጠበቅም በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የተገኘው 12 ሺህ ኩንታል ብቻ እንደነበረ የልዩ ወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም እንድሪስ አስታውሰዋል፡፡

ዘንድሮ ከ6 ሺህ 930 ሔክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን እና 187 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ከ3 ሺህ 900 ሔክታር የሚልቀው በማሽላ ሰብል መሸፈኑን ገልጸው፤ ከዚህም ከ105 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ ነው ያመላከቱት፡፡

ዘንድሮ የሚታየው የሰብል ሁኔታ የተሻለ መሆኑን አንስተው፤ ከዕቅድ በላይ ምርት እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በልዩ ወረዳው የተዘሩ ሰብሎች የተሻለ ምርት መስጠት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አሕመድ ጋሎ ናቸው።

በአጠቃላይ በዞኑ በዘንድሮው የምርት ዘመን ከ14 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል ሲሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በከድር መሀመድ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.