የጤና ባለሙያዎች ተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ሥርዓት በአዲስ መልኩ ሊሰጥ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጤና ባለሙያዎች ተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ሥርዓት በአዲስ መልኩ እንደሚሰጥ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።
ሚኒስትሯ አሁን ያለንበት ዘመን የህክምና ሳይንስ በከፍተኛ ሁኔታ ያደገበትና የቴክኖሎጂ ምጥቀት የታየበት ነው ብለዋል።
ጎን ለጎንም አዳዲስ አሰራሮችና አስተሳሰቦች የሰፈኑበት መሆኑን ጠቅሰው የኅብረተሰብ የጤና አገልግሎቶች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበት መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህን ከግምት ያስገባና ወቅቱን የሚመጥን የጤና ባለሙያዎች የሙያ ማጎልበቻ ሥርዓት መቅረጽና መተግበር እጅግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ገልጸዋል።
የሙያ ማጎልበቻ ሥርዓቱ አሁን ካለበት የተበጣጠሰና ደካማ አሰራር ወደተሻለና ወጥነት ወዳለው ሥርዓት ለማደራጀት በማለም የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሥርዓቱ በዋናነት የጤና ባለሙያውን ብቃትና ክህሎት ለማጎልበት ያለመ ቢሆንም የጤና አገልግሎቱን ጥራት በማሻሻል በኩል የማይተካ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።
የሙያ ማጎልበት ሥርዓት በሁሉም ደረጃና የሙያ ዘርፍ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን እውቀትና ክህሎት ከማሳደግ በተጨማሪ የሙያ እድገት ተወዳዳሪነትን ያሳድጋልም ነው ያሉት።
አሰራሩን ከጤና ባለሙያዎች የሙያ ፈቃድ እድሳት ጋር በማያያዝ ዋነኛው የብቃት ቁጥጥር መመዘኛ እንደሚሆን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሥርዓቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን መመሪያ መሠረት በማድረግ እንደሚተገበር የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸው እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው የሙያ ማጎልበቻ ሥርዓት በምን መልኩ ተፈጻሚ እንደሚሆን ሚኒስቴሩ በቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሏል።
የጤና ሚኒስቴር አሁን ያሻሻለው የጤና ባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ሥርዓት ከጥቂት ዓመታት በፊት ሥራ ላይ መዋሉ ይታወሳል።