Fana: At a Speed of Life!

በቀጣይ ጊዜያት የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ ለመኸር እርሻው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተያዘው የክረምት ወቅት የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ ለመኸር እርሻው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የብሄራዊ ሚትሪኦሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ቀደም ሲል የገባው ክረምት ሰኔ ላይ በተገቢው መንገድ መደበኛ የዝናብ ሁኔታ የተስተዋለበት እና አልፎ አልፎ ደግሞ ፀሀያማ ሁኔታ የነበረበት መሆኑን ኤጄንሲው ገልጿል።
ለተጀመረው የአመቱ የክረምት እርሻ ተስማሚ የነበረ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ግን ከመደበኛ በላይ ከፍ ያለ ዝናብ የተስተዋለበት አንደነበር ነው በኤጀንሲው የትንበያ እና ቅድመ ማስጠምንቀቂያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫሊ ደበሌ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።
ይህ የዝናብ ሁኔታ በተያዘው የክረምት ወራት ቀጣይ ጊዜያት ላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
ተጠናክሮ የሚቀጥለው የዝናብ ሁኔታ ለተያዘው የመኸር እርሻ ወቅት ወሳኝ መሆኑን ዳይሬክተሯ አንስተዋል።
ከመደበኛው ከፍ ብሎ የሚመጣው የዝናብ ሁኔታ በተለይም እንደ ጤፍ ላሉ ከፍ ያለ የውሃ መጠን ለሚፈልጉ ሰብሎች፣ ዘግይተው ወደ እርሻ ለገቡ እና የግጦሽ መሬት ለሚፈልጉ አካባቢዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚታሰብም ገልጸዋል።
ከመደበኛ ከፍ ያለ ዝናብ ምንም እንካን አወንታዊ ጎኖቹ ቢያመዝኑም፤ እስከዛሬ በዘነበው ዝናብ መሬቱ በቂ እርጥበት የያዘ በመሆኑ ወደ ቅፅበታዊ ጎርፍ የመቀየር አድል ስለሚኖረው አርሶ አደሩ እና የሚመከተው አካል ተገቢወን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ወይዝሮ ጫሊ ጠቁመዋል።
እስከ ዛሬ በነበረው የዝንብ ሁኔታ ጥሩ የሚባል የማሳ ዝግጅት እና የእርሻ ሁኔታ እንደነበረ ነው የገለጹት።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ በበኩላቸው እስከ ሀምሌ ወር አጋማሽ የብፅር ሰብሎች የሚዘሩበት ወቅት በመሆኑ ያለው የዝናብ ሁኔታ ተስማሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በአንዳንድ አከባቢዎች የዝናብ መጠኑ እየጨመረ በመምጣት አርሶ አደሩ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል።
በትእግስት አብርሀም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.