አቶ ሙስጠፌ መሐመድ የጅግጅጋ ነዋሪ ለኮሪደር ልማቱ ላሳየው ትብብር አመሠገኑ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለጅግጅጋ ኮሪደር ልማት ግንባታ የከተማዋ ነዋሪዎች ላሳዩት ቀና ትብብርና ድጋፍ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ምሥጋና አቀረቡ፡፡
ርዕሠ መሥተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ እና የከተማዋ አመራሮች በጅግጅጋ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ተመልክተዋል፡፡
አቶ ሙስጠፌ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ከተማዋን ውብ፣ ዘመናዊ፣ ከፍተኛ ኢኮኖሚ የምታመነጭ፣ ተመራጭ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ለተያዘው ራዕይ የኮሪደር ልማት ሥራው ወሳኝ ነው፡፡
ለዚህም መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
ለኮሪደር ልማቱ በተሠራው አዲስ ፕላንና ዲዛይን መሠረት የሚፈርሱ የንግድ ቤቶችና ተቋማት ይፋ መሆናቸውን ተከትሎ ነዋሪው ማንንም ሳይጠብቅ በፈቃደኝነትና በፍላጐት ሲያፈርስ ተመልክተናል ብለዋል፡፡
ይህም የከተማዋን ነዋሪዎች የልማት አጋርነትና ፍላጎትን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በከተማዋ 25 ኪሎ ሜትር መንገድ ያለው የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል የሆነ ዘመናዊው የሸቤሌ ሪዞርት፣ የመንገድ ግንባታዎችና ሌሎች መሠረተ-ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱን በስድስት ወራት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መሥተዳድሩ÷ ሥራውን በቀንና በምሽት እያሳለጡ ያሉ የፕሮጀክቱ ሠራተኞችን በማመስገን፤ በይበልጥ ሥራው እንዲፋጠን አቅጣጫ ሰጥተዋል።