ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የ796 ሚሊየን ብር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የ796 ነጥብ 90 ሚሊየን ብር (20 ሚሊየን ዩሮ) የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።
የገንዘብ ድጋፉም ለብሄራዊ ቤተ መንግስት እድሳት እና በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ የጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መለስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ የሚውል መሆኑም ታውቋል።
በዚህም ከ20 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ስምምነቱ ውስጥ 12 ሚሊየን ዩሮ ለብሄራዊ ቤተ መንግስት የመጀመሪያ ዙር እድሳት ድጋፍ የሚውል መሆኑንም የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የመጀመሪያ ዙር የቤተ መንግስት እድሳት መርሃ ግብርም ቤተ መንግስቱን በማደስ ለህዝብ ክፍት ማድረግን የሚያካትት መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ሁለተኛው የድጋፍ ስምምነት ማለትም 8 ሚሊየን ዩሮው ደግሞ በግብርና ትራንስፎርሜን ኤጀንሲ በኩል በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ የጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መለስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የሚውል መሆኑም ታውቋል።
በዚህ መርሃ ግብርም የ1 ነጥብ 8 ሚሊየን አነስተኛ አርሶ አደሮችን እንዲሁም በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ 1 ሺህ 340 የጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መለስተኛ ኢንተርፕራይዞችን የምርት አቅም እና ገቢ ለማሳደት እንደሚረዳም ይጠበቃል።
የድጋፍ ስምምነቱንም የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ቫሊር ቴሂዮ በቪዲዮ ክንፍረንስ በመታገዝ ፈርመውታል።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይም በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር እና በአፍሪካ ህብረት የፈረንሳይ ተወካይ ፍሬድሪክ ቦንቴምስ ተገኝተዋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።