ከውጭ አገር የሚመጣ መንገደኛ በ72 ሰዓታት የሚጠበቅበት የኮቪድ ምርመራ ማረጋገጫ ወደ 5 ቀን ከፍ ማለቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 9 ፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ መንገደኛ በ72 ሰዓታት ውስጥ ተመርምሮ ከኮቪድ ነፃ የሚል ማረጋገጫ እንዲያመጣ የሚያስገድደው መመሪያ ወደ አምስት ቀናት ከፍ አለ።
የሚኒስትሮች ኮሚቴ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅታዊ ሁኔታና ቀጣይ አዝማሚያ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ዛሬ ተወያይቷል።
ከዚህ ቀደም ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ ማንኛውም ዜጋ በ72 ሰዓት ጊዜ ውስጥ ተመርምሮ ከኮቪድ ነፃ የሚል ማረጋገጫ ሲኖረው ወደ አገር ቤት መግባት እንደሚችል ነገር ግን በቤቱ ለ14 ቀናት እንደሚቆይ የሚደነግግ መመሪያ ወጥቶ ነበር።
ከውጪ የሚመጡ ዜጎች የምርመራ ውጤት ካልያዙ ለሰባት ቀን ወደ ለይቶ ማቆያ እንደሚገቡም ይታወቃል።
ዛሬ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳስታወቁት÷ በበርካታ አገራት ምርመራው ጊዜ የሚወስድ እና መንገደኞችም በቶሎ ምርመራውን አድርገው ውጤቱን ይዘው መምጣት እንዲችሉ እና መንገዱ የሚፈጀው ጊዜ ታሳቢ ተደርጎ መሻሻል እንዳለበት አንስተዋል።
ባሉበት አገር ተመርምረው ኢትዮጵያ እስከሚገቡ ከሶስት ቀናት በላይ ይወስድብናል የሚል ቅሬታ ከተለያዩ መንገደኞች በመምጣቱ ነው ማሻሻያው የተደረገው ብለዋል።
ይሁን እንጂ በአንድ በኩል ውጤቱ በጣም ከቆየ ያንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እና የመከላከል ስራውን በማያደናቅፍ ሁኔታ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ነው ያሉት ።
ይህ በመሆኑ ከቴክኒክ ቡድን እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ 72 ሰዓታት ተብሎ የተቀመጠው ወደ አምስት ቀን እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።
ይህ በመሆኑ በአምስት ቀናት ውስጥ የተደረገ የምርመራ ውጤት ይዘው የሚመጡ መንገደኞችን አየር መንገድ ሲደርሱ ናሙና እየተወሰደ የ14 ቀናት የቆይታ ጊዜያቸውን በቤታቸው እንዲቆዩ መደረጉ የተሻለ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።